Published using Google Docs
የሰማዕታቱ የጩኸት ደም.doc
Updated automatically every 5 minutes

የሰማዕታቱ ደም ጩኸት

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።

አቤቱ የሠራዊት አምላክ እግዚአብሔር ሆይ ይህ  ጉባኤ እውነትን የሚመለክት በእውነት ላይ የሚቆም አድርገው። እውነት መንገድና ሕይወት አንተ ነህና በሚደነቅ ክብርህ አስተባብረው ፣ የጥንቱን የአባቶቻችንን መንፈስ አድለው፤ በዓላማ የሚጓዝ እቅድ ያለው አድርገው።አሜን

“እስመ ኢኮነ ትምህርትነ ለስሂት ወኢዘርኩስ ወኢኮነ ዘጽልሁት። ዳእሙ በዘአመከረነ እግዚአብሔር ወተአመነነ በትምህርተ ወንጌሉ ከማሁ ንነግር ወአኮ ከመ ዘለሰብእ ያደሉ ዘእንበለ ለእግዚአብሄር ዘአመከረነ ልበነ
1 ተሰ 2፡3-4

“ልመናችን ከስሕተት ወይም ከርኩሰት ወይም ከተንኮል አልነበረምና ነገር ግን ወንጌልን አደራ ይሰጠን ዘንድ እግዚአብሔር የታመንን ሆነን እንዳገኘን መጠን እንዲሁ እንናገራለን፤ ልባችንን የሚመረምር እግዚአብሔር እንጂ ሰውን ደስ እንደምናሰኝ አይደለም”   1 ተሰ 2፡3-4

ካንደበታችን የሚወጣው በተግባር የምንገልጸው በተሳሳተ መንገድ በጥላቻ አይደለም። ማንንም ሰው ለመጉዳት ለማሳዘንና ለማስከፋት ለመደግፍና ለማስደሰትም አይደለም።  ጩኸታችን ”ኢትትቤቀሎሙኑ ወኢትኴንኖሙኑ  በእንተ ደምነ  እምእለ  ይነብሩ ዲበ ምድር” “በታላቅ ድምፅ እየጮኹ ቅዱስና እውነተኛ ጌታ ሆይ እስከመቸ ድረስ አትፈርድም?ስለ ደማችንስ በምድር በሚኖሩት ላይ እስከ መቼ አትበቀልም?”  እያሉ የሚጮሁትን ጩኸት ለማስተጋባት እነሱ የሚከሱትን ድምጽ ለማሰማት ነው።

“ኢኮነት ዛቲ ጥበብ እንተ እምላዕሉ ትወርድ አላ እምድር እንተ እምነፍሰ አጋንንት። እስመ ኀበ ሀለወ ተቃንኦ ህየ  ወሀለወ ሀውክ ወካህድ ወኩሉ እከየ ምግባር። ወእንተሰ እምላዕሉ ጥበብ ቀዳሚሃ ንጽህት እንተ ታስተሰናኡ::”( ያዕ 4፡17) ይህች እስካሁን ዓለም የሄደችበት   ጥበብ ምድራዊት አጋንንት ከተወሀዳቸው ሰዎች የምትፈልቅ ናት። ይህች ጥበብ የአራዊት  የአረመኔዎች የጨለማው ገዥ ሰራዊቶች ናት።

የጠላት ዲያቢሎስ መመሪያ  መለያየት ማለያየት፣ መጣላት ማጣላት፣  መከፋፈል መግደል.፣ ማሳደድ ማሰር መዝረፍ እና የመሳሰሉት  ነው። ይህ  እንዲተገበር ሌት ተቀን መግፋት፣  እቅድ መንደፍ ፣ በትጋት መሥራት የተካነበት ነው።  ይህንን ለማሸነፍ የሚቻለው  ኦሆ በልዎ ለእግዚአብሔር፤  ወእንብየ በልዎ ለጋኔን። ወይ ጎይይ እምኔክሙ። ቅረብዎ ለእግዚአብሔር ወይቀርበክሙ“ “እንግዲህ ለእግዚአብሔር ተገዙ ፣ ዲያቢሎስን ተቃወሙ።”(ያዕ 4፡7)የሚለውን በመከተል  ከላይ የጠቀስናቸውን የዲያቢሎስ መርሆ  አንጋቢዎች የሚሰብኩትን አትስሙ፣  የሚያቅዱትን አትቀበሉ  በማለት ቤተ ክርስቲያን ታስተምራለች።  የእግዚአብሔር  ፈቃድ  የሆነውን የሚያዋድደውን የሚያፋቅረውን የሚያከባብረውን የሚናገረውን መልእክት ስሙ ተከተሉ ትላለች።  

በዚህ ተመርኩዘን በቤተ ክርስቲያን የገባውን ጸብ ለማስወገድ እርቅ ሞከርን ያገኘነው መልስ እርቅ የሚሉ ሁሉ ይወገዱ፣ ይገደሉ  የሚል ነው። ቤተ ክርስቲያናችን በዚህ አይነት መልክ ተከፋፍላ ተዳክማ እያለች፣ እረኞች  ተዘናግተው እያሉ መንጋው በየአቅጣጫው እየተበተነ፣ እየመነመና እያለቀ ይገኛል ።  ከደረሰበትም ሰቆቃ ለመሸሽ ዛሬ በየብስና በባሕር መሰደድን አማራጭ አድርጎ  ይገኛል።

ሀገራችን ኢትዮጵያ በመልካም አስተዳደር እጦትና ጉድለት የተነሣ ለህዝቧ የማትመች የምድር ሲኦል በመሆኗ ወገኖቻችን የተሻለ ህይወት ፍለጋ ስደትን መፍትሔ አድርገው አውራ እንደአጣ ንብ በመቅበዝበዝ በዓለም መበተናችን የታሪካችን ክፍል ሆኗል። የዚህ ስደት ውጤት   በዱር አራዊት መበላት ፣ በሰው መሰል እንደ አይሲሲ አይነት አውሬዎች  እና   አረመኔዎች  እጅ እየወደቁ መታረድና የውቅያኖስ አሳ አንበሪ ቀለብ መሆን ነው።

ይባስ ብሎ ደግሞ  በዚህ ወቅት በመንበሩ ላይና አካባቢ ያሉ ሰዎች ከመንግሥት እየተቀበሉ መንግስት የሚያስረውን ሁሉ ታራሚ በማለት እየፈረጁ  ሲናገሩ ይሰማል።  ይህ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ  ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ድምጽ አይደለም።

ቤተ ክርስቲያን ካንድ ወግኖ የፈረጀውን አንዱን ወግኖ የሰጠውን ብቻ በመቀበል ታራሚ አንዱን አራሚ አድርጋ አትፈርጅም። ቤተ ክርስቲያን በታቦቱ ላይ ያለውን ታውጃለች። የታቦቱ መልእክት “እናንት ሰው መሳይ አራዊት አረመኔዎች ፣ ኦሪቱ ውስጥ ያላችሁ ሁሉ በእግዚአብሔር አርአያ የተፈጠረውን የሚመስላችሁን ሰው አትግደሉ፣ አታስበርግጉ፣ በሰፈራችሁው ቁና እንዳትሰፈሩም በእናንተ ላይ ሊደረገባችሁ  የማትፈልጉትን በሌላው ሰው ላይ አታድርጉ ነው።  

“ኢኮነት ዛቲ ጥበብ እንተ እምላእሉ ትወርድ አላ እምድር እምነፍሰ አጋንንት“ ማለትም  አጋንንት ከተዋሀዳቸው ደም ከሚያፈሱ እና ከሚያስፈስስሱ ሰዎች ንክኪ ንግግር አመራር መራቅ ነው።   “ወእንተሰ እምላዕሉ ጥበብ ቀዳሚሃ  ንጽህት ይእቲ እንተ ታስተሳንኡ ኦ ሆ በሀሊት ወምልእት ምህረተ ወፍሬሃ ሠናይ ዘእንበለ ኑፋቄ አማኒት” ሲተረጎም የምታስማማ ፣ የምታስታርቅ፣ የምታዋድድ ፣ የምታከባበር፣ የምታስተዛዝን ፣ የምትታረቅና የምታስታርቅ ፍሬዋ ለሰው ልጅ የምትጠቅመውን ጋኔን እምቢ የምታሰኝ እግዚአብሔርን ”ኦ ሆ!” አሰኝታ የምታስገድድ ናት። ነገር ግን አሁን ባለበት የሚቀጥል ከሆነ  “ኦ ሆ በልዎ ለእግዚአብሄር ወእንብየ በልዎ ለጋኔን ወይጎይይ እምኔክሙ”(ያዕ 4፡7)። ለእግዚአብሄር የሚቀርበው ኦሆታ፤ ለጋኔን የሚቀርበው እምቢታ፤ መልኩ እና አቅጣጫውን ቀይሮ  የርስ በርስ መጠፋፊያ እንዳይሆን ቤተ ክርስቲያን ታስጠነቅቃለች። በመጨረሻም አብርሃም ልጁን ለመስዋዕትነት ያቀረበላት፤ ያዕቆብ በፍኖተ ሎዛ የተመለከታት መሰላል፤ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቀራኒዮ መስቀል ላይ ደሙን ያፈሰሰላት፣  ቅዱስ ጴጥሮስ ቁልቁሊት የተሰቀለላት ፣ ቅዱስ ጳውሎስ በሮም አደባባይ የተሰየፈላት፤ ተሳቱ ቅዱሳን የተሰደዱላት(የተሰደዱባት) ፣ ቅዱስ ያሬድ ርእክዋ ነፀርክዋ ተሳለምክዋ አፍቀርክዋ እያለ በጣዕመ ዜማው የአቀነቀነላት፤ ነቢዩ መሐመድ ሐበሻ (ኢትዮጵያ) የእውነት ሀገር እንደሆነች የመሠከሩላት፤ ሚያዝያ ፲ ቀን ፳፻፯   (ኤፕሪል ፲፱ ቀን ፪ሺ፲፭ ዓ.ም) በባሕረ አድርያ የሕይወት መስዋዕትነት ከፍለው አሻግረው የተመልከቷት፤ ወደ ኢየሩሳሌም ሰማያዊት የምታገባ ብቸኛዋ በእነዚህ ሰማዕታት ታየች ተገልጸች፣ ተረጋገጠች።  ስለሆነም ከዚህ የሚከተለውን ማሳሰቢያ አቀርባለሁ።

፩. የዓለም ሕዝብ ሆይ ከርኩሰትህ ተመልስህ በተዋሕዶ የከበረ ክርስቶስን ተመልከት።        

     ኤፌ ፬፤-፲፱።ሮሜ ፩፦፳፮--፳፰።

፪. ኢትዮጵያዊ ወገኔ ይህ ሁሉ መከራ ሰቆቃ ውርደት መገፋት መናቅ ለምን ተፈራረቀብህ? ከሕይወት ጉዞህ ከታሪክ ከቅዱሳት መጻሕፍት መልሱን ታገኛለህ። ወደ ኋላና ወደ ፊት ተመልከት።ባሩድ አልባ ቀለህ ይዘህ የትም አትደርስም። ብሔራዊ ኑዛዜ፣  ብሔራዊ እርቅ እና ብሔራዊ ይቅርታ በግልም በማኅበርም ካላወጅክ የገነባኽው ይደረመሳል። የአነጽከው ይፈርሳል፤ ትውልድ አልባ ታሪክ አልባ እንዳትሆን ተጥንቀቅ።   ”የቆመ የሚመስለው እንዳይወድቅ ይጠንቀቅ “ ተብሎ ተጽፏልና።የአሳለፍከው ፵ ዓመታት ትምህርት ይሁኑህ። ዛሬ በሥልጣን ላይ ሆነህ ሥልጣንህን መከታ አድርገህ የምታሥር፤ የምትገርፍ፣ የምታሰቃይ፣ የምትገልና የምታስገድል “ አግባዓ ለመጥባህትከ ወስተ ቤታ ዘቀተለ በመጥብህት ይመውት በመጥባህት” በማለት መለኮታዊ ኃይለ ቃል ያዳኝብኃል። በተጨማሪም ነገ አንተም የጅህን እንድምታገኝ ከታሪክ ተማር። እሥራትና ግድያን አቁምህ ወደ ህሊናህ ተመለስ። መሣርያ ያነገብክ ሁሉ በጠረጴዛ ዙርያ ተቀመጥ። ቤተ ክርስቲያን ግን እነ አቡነ አኖርዎስ ፊልጶስ እንዲሁም ሰማዕቱ አቡነ ጴጥሮስን አብነት በማድረግ “ዘይትዌከፎሙ ለዕለ ይስደዱ ረዳኢወለዕለ ውስተ ሠርም ይትመነደቡ መድኅን ለርኁባን ዘይኄሊ ወይትቤቀል ለግፉዓን አርከ መሕይምናን መስተናግር ለጻድቃን “ ሲተረጎም   “የትሁታንን ሰውነት የሚጎበኝ የተቸገረውን ሰውነት ቸል የማይል ከሀገራቸው የተሰደዱትን የሚያድን ለተራቡት የሚያስብላቸው  ለተበደሉ የሚበቀልላቸው” መ/ኪ ፬፻፶፪፦፪--፫ የአለውን በመጸለይ ብቻ ሳይሆን በተግባር በመተርጎም  ከሚታሠረው ከሚሰደደው ከሚሞተው ከሚራበው ከሚጠማ ጋር አብራ ትቆማለች።

                                            “ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር”

“ወስብሐት ለእግዚአብሔር”

ሊቀ ማእምራን ቀሲስ ዶ/ር አማረ ካሣዬ

ግንቦት ፪ ፳፻፯