Published using Google Docs
ገብር ኄር (የዐቢይ ጾም 6ኛ ሳምንት)
Updated automatically every 5 minutes

ገብር ኄር (የዐቢይ ጾም 6ኛ ሳምንት)

 

የዕለተ ሰንበት መዝሙር (ከጾመ ድጓ)

 

መኑ ውእቱ ገብር ኄር ወምእመን ዘይረክቦ እግዚኡ በምግባረ ሠናይ ወይሠይሞ ዲበ ኲሉ ንዋዩ ካዕበ ይቤሎ እግዚአብሔር ገብር ኄር ወምእመን ዘበውኁድ ምእመነ ኮንከ ዲበ ብዙኅ እሠይመከ ባእ ውስተ ፍሥሐሁ ለእግዚእከ፡፡

ትርጉም:

ጌታው በመልካም ሥራ የሚያገኘው በሐብቱ ኹሉ ላይ የሚሾመው፤የታመነ በጎ አገልጋይ ማን ነው? ዳግመኛም እግዚአብሔር አንተ የታመንክ በጎ አገልጋይ በጥቂቱ የታመንህ ስለኾንህ በብዙ እሾምሃለሁ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ ይለዋል::

 

መልዕክታት

 

2ኛ ጢሞ.2÷1-15

“ ልጄ ሆይ÷ አንተም በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ በርታ፡፡ በብዙ ምስክሮች ፊት ከእኔ የሰማኸውን ትምህርት ለሌሎች ሊያስተምሩ ለሚችሉ ለታመኑ ሰዎች እርሱን አስተምራቸው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስን እንደሚያገለግል በጎ አርበኛ ሆነህ መከራ ተቀበል፡፡…”

1ኛ ጴጥ.5÷1-11

“ እንግዲህ እኔ ከእነርሱ ጋር ሽማግሌ÷ የክርስቶስም መከራ ምስክር÷ ደግሞም ሊገለጥ ካለው ክብር ተካፋይ የሆንሁ በመካከላቸው ያሉትን ሽማግለዎችን እማልዳቸዋለሁ፡፡ በእናንተ ዘንድያሉትንየእግዚአብሔርን መንጋዎች ጠብቁ፤ ስትጠብቁአቸውም እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በውድ እንጂ በግድ አይሁን፤ በበጎ ፈቃድ እንጂ መጥፎውን ረብ በመመኘትም አይሁን፡፡…”

 

ግብረ ሐዋርያት

 

የሐዋ.1÷6-8

 “እነርሱም ተሰብስበው ሳሉ÷ "ጌታ ሆይ÷ በዚህ ወራት ለእስራኤል ልጆች መንግሥትን ትመልሳለህን?” ብለው ጠየቁት፡፡ እርሱም መልሶ እንዲህ አላቸው÷ “አብ በገዛ ሥልጣኑ የወሰነውን ቀኑንና ዘመኑን ልታውቁ አልተፈቀደላችሁም፡፡ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በወረደ ጊዜ ኅይልን ትቀበላላችሁ፤በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ሁሉ፣በሰማሪያና እስከ ምድር ዳርቻ ድረስም ምስክሮቸ ትሆኑኛላችሁ።"

 

ምስባክ

መዝ. 39÷8

"ከመ እንግር ፈቃደከ መከርኩ አምላኪየ፡፡ ወሕግከኒ በማዕከለ ከርሥየ፡፡ ዜኖኩ ጽድቀከ በማኅበር ዐቢይ፡፡"

ትርጉም፦

 

 አምላኬ ሆይ፥ ፈቃድህን ለማድረግ መከርሁ፥ ሕግህም በልቤ ውስጥ ነው። በታላቅ ጉባኤ ጽድቅህን አወራሁ::”

 

ወንጌል

ማቴ. 25÷14-30

 “መንገድ እንደሚሄድ÷ አገልጋዮቹንም ጠርቶ ሊያተርፉበት ገንዘቡን እንደ ሰጣቸው ሰው እንዲሁ ይሆናልና፤ ለእያንዳንዱ እንደ ችሎታው ለአንዱ አምስት÷ ለአንዱ ሁለት÷ ለአንዱም አንድ ሰጠና ወዲያውኑ ሄደ፡፡ ”

 

ገብር ኄር (ታማኝ አገልጋይ)

 

የዓቢይ ጾም ስድስተኛው እሑድ

 

“አንተ በጎ ታማኝ ባሪያ፤ በጥቂቱ ታምነሃል፥ በብዙ እሾምሃለሁ፤ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ፥” (ማቴ.25፥14-30)

 

ገብር ኄር፦ ሥርዎ ቃሉ ግእዝ ሲሆን፥ ገብር ማለት አገልጋይ፥ ኄር ደግሞ ታማኝ፥ ቸር፥ ትኁት ማለት ነው። ቀጥተኛ ትርጉሙም ታማኝ አገልጋይ (ባሪያ) ይሆናል። ባር (ዕብ) ማለት ልጅ ሲሆን ያ (ዕብ) ደግሞ ያዌ (ያሕዌ) የሚለው የእግዚአብሔር ስም ነው። ትርጉሙም የእግዚአብሔር ልጅ ማለት ነው።

የጾመ ዐቢይ ስድስተኛው እሑድ ገብር ኄር የተባለው ጌታ በምሳሌ ያስተማረውን፥ ሐዋርያው ማቴዎስ በወንጌሉ ዘግቦ ያስቀመጠውን የአንድ አገልጋይ ታሪክ መሠረት ተደርጎ ነው። አገልጋዩም፥ ጌታው በእምነት የሰጠውን መክሊት በደስታ ተቀብሎ እንዲመልስም በተጠየቀ ጊዜ አትርፎ ስላስረከበ፥ “አንተ በጎ ታማኝ ባሪያ፤ በጥቂቱ ታምነሃል፥ በብዙ እሾምሃለሁ፤ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ፥” (ማቴ.25፥14-30) ብሎ በማመስገን የሾመው ታማኝ አገልጋይ ሰው እምነታዊ ግብር የሚነሳበትና የሚነገርበት ስለ ሆነ ገብር ኄር የሚለው ስያሜ ተሰጥቶታል። ከትምህርቱ ምሳሌ እንደምንገነዘበው (ገብር ኄር) ታማኝ አገልጋይነት  ከመክሊት እና ከታለንት ጋር ተዛምዶ እንዳለው ነው። ከዚህም በመነሳት ከሁሉ አስቀድመን ልንጠይቅ የሚያስፈልጉን ሁለት ጥያቂዎች አሉ። የመጀመሪያው “መክሊት ምንድር ነው?” ሁለተኛው ደግሞ “እንደ ክርስቲያን በግለሰብ ደረጃ እግዚአብሔር ለእኔ የሰጠኝ መክሊት ምንድር ነው?” የሚሉት ይሆናሉ። (2ኛ ጢሞ.2፥1-16፤ 1ኛ ጴጥ 5፥1-12፤ ሐዋ.1፥6-9፤)

መክሊት፦ የክብደት መለኪያ፥ ገንዘብ፥ ሀብት፥ ንብረት፥ ስጦታ፥ አደራ፥ ወዘተ… ይሆናል። በተጨማሪም ማንኛውንም አይነት እውቀት፥ ጥበብ፥ ችሎታ፥ ጊዜ፥ ጉልበት፥ ትጋት የተመቻቹ ሁኔታዎችን ወ.ዘ.ተ… ሁሉ ይወክላል።  ማንም ሰው እንደ አማኝ የእኔ ብሎ በኩራት በመንጓደድ ሊመጻደቅበት የሚችለው አንድም መክሊት የለም። ይሁንና አንድ ሰው አንደበቱን አላቅቆ የእኔ ነው ሊል የሚችለውና ከእግዚአብሔር ያልሆነ ነገር ቢኖር ከአባቱ ከአዳም የወረሰው ኃጢአት ብቻ ነው። መክሊት (አገልግሎት) ብዙ ትርጉምና ፈርጅ ያለው፤ ለማንኛውም ምዕመንና ምዕመንት በእግዚአብሔር የሚሰጥ የጸጋ ስጦታ ነው። (ማቴ.25፥15) “የጸጋም ስጦታ ልዩ ልዩ ነው፤ መንፈስ ግን አንድ ነው። አገልግሎትም ልዩ ልዩ ነው፤ ጌታም አንድ ነው፤ አሠራርም ልዩ ልዩ ነው። ሁሉን በሁሉ የሚያደርግ እግዚአብሔር ግን አንድ ነው።” (1ኛ ቆሮ.12፥4-6)  ቸሩ አምላክ በአንድ መንገድ በሌላም ለእያንዳንዱ ሰው እንደየአቅሙና እንደየችሎታው የራሱ የሆነ የመክሊት ወይም የታላንት ስጦታዎችን ይሰጣል። ስጦታዎቹም ሥጋዊ ወይም መንፈሳዊ ሊሆኑ ይችላሉ። (1ኛ ቆሮ፥12፥7-11)በመንፈሳዊው መንገድ ለመንፈሳዊ ሥራ የሚሰጡ የጸጋ ስጦታዎች  ተብለው ይታወቃሉ። የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች ሁሉ መክሊቶች ናቸው። መክሊትን ከቤተ ክርስቲያን በሹመት፥ በሥልጣንና በማዕረግ ብቻ የሚሰጥ አድርገን የምንቆጥር ጥቂት አይደለንም። አዎን ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የምትሰጠው ሹመት፥ ሥልጣንና ማዕረግ አለ። ይሁንና ግን አንድ ምዕመን ወይም ምዕመንት ደግሞ እንደ ክርስቲያንነቱ ከእግዚአብሔር የተሰጠው የራሱ የሆነ መክሊት አለው። ቤተ ክርስቲያን ሥልጣን በሹመት የሰጠችው ሆነ ያልሰጠችው ምዕመንና ምዕመንት ሁሉ በተሠማራበት ሥፍራ ሁሉ ባለ መክሊት ነው። እግዚአብሔር በሰጠው ማንኛውም ነገር አስተማሪው፥ ገበሬው፥ ባንከኛው፥ ጠበቃው፥ ዶክተሩ፥ ኢንሹራንስ ሻያጩ፥ የመንግሥት ሆነ የግል ሠራተኛው ሁሉ ሙያው መክሊቱ ነው። ይህንምም አውቆ መክሊቱን በእውነትና በሐቅ ሊጠቀም ይገባዋል።

ለምሳሌ ያህል አንድ ክርስቲያን በንግድ ሥራ የተሠማራ ቢሆን እንደ ክርስቲያንነቱ በንግድ ሥራው ላይ የሚጠበቅበት አገልግሎት አለ። ምንም እንኳን ለትርፍ የተቀመጠ ቢሆንም በነጻ ገበያ ወይም በአቅርቦትና ፍላጎት ስም ካለ አግባብ የተጠቃሚን ኪስ ሊገለብጥ አይገባም። እንዲሁም በሌላ የሥራ ዘርፍ የተሠማሩ በተቀጠሩበት ሙያ ሕዝብ በጉቦና በሙስና፥ በረባ ባልረባው ማመላለስና ማጉላላት እግዚአብሔርን ማስከበር ወይም ሰውን መጥቀም አይደለም። ራስን ማገልገልና ራስን መጥቀም፥ መክሊትንም ከመቅበር ይቆጠራል። ክርስቲያናዊም አይደለም።  ይህንም ካለማወቅና ካለማስተዋል የተነሳ ብዙ ምዕመንና ምዕመንት መክሊት፥ አገልግሎት በቤተ ክርስቲያን የሚሰጥ ሹመት፥ ሥልጣንና ማዕረግ አድረገው ይወስዳሉ። ይህ ብቻ አይደለም በቤተ ክርስቲያን አካባቢ፥ እምነት ነክና ቀመስ ነገር ብቻም ላይ የተወሰነ አድርገው ይቆጥራሉ። ግን አይደለም። አገልግሎት በጊዜ ወይም በስፍራ አይወሰንም። አገልግሎት የሚሰጠው የእግዚአብሔርን ስም ለማስከበር እና ለሰዎች ጥቅም ስለ ሆነ በማንኛውም ወቅትና ቦታ ሁሉ አገልግሎታችን እምነትና ሐቅን የተሞላው ሆኖ ሊገኝ ይገባዋል።

ለምሳሌ ያህል ባልነትን፥ ሚስትነትን፥ ልጅነትን፥ ሠራተኛነትን ወ.ዘ.ተ… የአገልግሎት መስክ አድርገው የማይቆጥሩ ክርስቲያኖች ቁጥር ጥቂት አይደለም። ባል በጌታ የተሰጠውን የቤት ራስ አባዋራነቱን አክብሮ ተቀብሎ ሚስቱን እንደ ራሱ አድርጎ መውደዱን ከመክሊት (አገልግሎት) ካልቆጠረ፤ ሚስት ለባሏ በፍቅር ተገዝታ የልጆች የበላይ የቤቷ እመዋራ መሆኗን ከመክሊት (አገልግሎት) ካልቆጠረች፤ የአገልግሎት ምንንነት ገና አልተረዱም። ከሁሉም አስቀድሞ መክሊት (አገልግሎት) ለትርፍ ወደ አደባባይ ከመውጣቱ በፊት የሚጀምረው የአገልግሎት ሁሉ እምብርት ከሆነው ከራስ ቤት፥ ከትዳር እንደ ሆነ መረዳት የሚጎድለን ጥቂት ሰዎች አንጠፋም። አንዳንድ ወንዶች በቤት ውስጥ የሚከወን ማንኛውንም ነገር ከውድ ሚስቶች ትካሻ ላይ እርግፍ አድርገው የቴሌቭዥን፥ የኢንተርኔት ወ.ዘ.ተ... አባዋራ ይሆናሉ። ሚስት ከማጀት ደፋ ቀና ስትል እርሱ ሶፋ ላይ ተቀምጦ የጣቢያ መቀየሪያ ከፍ ዝቅ ያደርጋል። አንዳንዱም የበላበትን ሳሐን ማጠብ ይቅርና ከጠረጴዛ ላይ የማያነሳም ባል አለ። በትዳር ዓለም የቤት ውስጥ የዕለት ከዕለት ግብር በአንድ ሰው ትካሻ ላይ የቆመ አይደለም። ባሎች ሚስቶችን ሊያግዙና ሊረዱ የውዴታ ግዴታ አለባቸው። ይህንም ስል፥ “ውሀ ውስጥ የሚጨመር ክሎሪን የእጅ ቆዳ ላይ ንቃቃት አስከትሎ ያቆረፍዳል” በሚል ፈሊጥ ማጀት ባዕድ የሆነባቸው ሰነፍ ሚስቶችም እንዳሉ አይዘነጋም። ባል ለሚስት፥ ሚስት ለባል የሚያሳዩት ፍቅር፥ መተሳሰብና አንድነት ለእርስ በርስ የሚሰጥ ታላቅ አገልግሎት እንደ ሆነ አንዘንጋ። የእነርሱ ትዳር ለሌሎች አርአያ ሊሆን እንደሚችል መዘንጋት የለበትም። አንዳንድ ምዕመንና ምዕመንት ደግሞ የቤታቸው ምድጃ ተዳፍኖ፥ ክፍሎች በቅዝቃዜ ጽልመት ተውጠው የቤተ ክርስቲያንን ብርሃን ለመሆን የሚጥሩ አሉ። በግለሰብ ደረጃ አገልግሎት ከራስ ቤት ይጀምራልና ቅድሚያ የሚሰጠውን አገልግሎት ጠንቅቀን እንወቅ። ከቤት የጀመረ ቅንና ታማኝ አገልግሎት ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲወጣ የማስመሰል ጨንበል አይታይበትም። የአገልግሎት ሚሥጥር ስለተገለጠለት፥ ትርጉሙም ስለገባው አንካሳና ግብዝ፥ ሁለት ፊት ያለው አገልግሎትን ለእግዚአብሔር አይሰጥም፤ ለሰዎች ታይታም አያቀርብም። ሌላው በሥራ ቦታ የሚደረግና የሚሰጥ አገልግሎት ነው። ማንም ክርስቲያን በተሠማራበት ማንኛውም አይነት የሥራ ዘርፍ የአሠሪን ሰዓት፥ ሐብት፥ ንብረት በምንም አይነት መንገድ ካለ አግባብ መጠቀም ወይም መውሰድ አገልግሎትን ማበላሸት እንደ ሆነ ሊገነዘብ ይገባል። አንድ ክርስቲያን የትም፥ ከማንም ጋር በታማኝነትና በእውነት ማገልገል ይጠበቅበታል።

በተጨማሪ አገልግሎት ብዙ ዘርፎች ያሉት በማንኛውም የሙያ ዘርፍ ውስጥ የሚገኝ፥ በውጤቱም ለእግዚአብሔር ክብርንና ለሰዎች ጥቅም ማስገኘት ማለት ነው። ለምሳሌ መካኒኩ በመካኒክነቱ፥ ጠበቃው በጠበቃነቱ፥ ዶክተሩ በዶክተርነቱ፥ መሀንዲሱ በመሀንዲስነቱ፥ አንጥረኛው በአንጥረኛነቱ ወ.ዘ.ተ... አገልግሎቱን በእምነትና በታማኝነት ከሰጠ ታማኝ አገልጋይ፥ ታማኝ ባርያ ነውና ጌታ በምሳሌው እንዳቀረበው ሽልማቱንም ፈጽሞ አያሳጣምው፤ አያጎድልበትምም። እግዚአብሔር በቸርነቱ በመክሊትነት በአደራ የሰጠንን ሐብትና ንብረት፥ የለገሰንን እውቀት፥ የሰጠንን ጤንነት ተጠቅምን፥ ሰዎችን ከጠቀምን የአገልግሎት ትንሽ የለውም። በሽተኞችን፥ እስረኞችን መጠየቅ፤ መምከር፥ የተጣሉን ማስታረቅ፤ ችግረኞችን መርዳት፥ መመጽወት ወ.ዘ.ተ... እኒህንና የመሳሰሉት ሁሉ የአገልግሎት ዘርፎች ናቸው። (ማቴ.25፥40) በተሰጠ ሙያ በእውቀት፥ በምክር፥ በማስታረቅ፥ ሰላምን በመፍጠር፥ በጉልበት፥ በትጉ ሠራተኛነት የምንመደብበትና የምንቀጠርበት የሥራ ዘርፍ ሁሉ መክሊት ነው። በታማኝነትም የማገልገል አደራና ኃላፊነት አለብን። ለብዙዎች የሚያስቸግረን ዋናና ተቀዳሚ ነገር የመክሊትን ትርጉም በመረዳት በእጃችን የያዝነውን መክሊት ማወቁ ላይ ነው። መክሊት ደግሞ  በጌታ በራሱ ብቻ የሚሰጥ ስለ ሆነ እንደ ሕያው ቃሉም ጌታ እንደ ፈቀደ፥ እንደ ፈለገና እንደ ወደደ ለአንዱ አምስት፥ ለሌላው ሁለት፥ ለሌላው ደግሞ አንድ ይሰጣል።

እግዚአብሔር አቅማችንን ያውቃል። ማንነታችንን ያውቃል። ምን ማድረግ እንደምንችልና እንደማንችል ስለሚያውቅም እንደ የአቅማችን፥ እንደ የችሎታችን ለአንዱ ከፍ፥ ለሌላው ደግሞ ዝቅ አድርጎ ይሰጣል። ብዙም ይሁን ጥቂት የተሰጠውን በጥበብ በአግባብ የመጠቀም ጉዳይ ግን የተሰጠው ግለሰብ አመለካከት ይወስነዋል። አገልግሎት ማለት ከራስ ያለፈ፥ ግን ለሌሎች በፍቅር፥ በነጻነት፥ በፈቃድ የሚደረግ፥ የሚሰጥ እምነት ያለው ግብር ነው። አገልግሎት መጠን፥ ጊዜና ቦታ አይወስነውም። አንድ አገልጋይ በእግዚአብሔር ፊት በፍርሃት የሚንቀጠቀጥና ፈቃደኛ ልብ ካለው፤ (መዝ..2፥11) በእግዚአብሔር በመታመን ከእርሱ ጋር ከተጣበቀ፤ (ማቴ..6፥24) በመንፈስ ቅዱስ ሙላት ለመመራት ፈቃደኛ ከሆነ፤ (ሮሜ.7፥6) የተዋረደ ልብ እና (ሐዋ.20፥18-19) ለሌሎች ፍቅርን ካሳየ (ገላ.5፥13) በማያጠራጥር ሁኔታ በአደራ ለተሰጡትን መክሊቶች ትርፍ ያገኝባቸዋል። የገብር ኄርን የታማኙን አገልጋይ ታሪክ ሙሉ ለሙሉ ስናነብ በፍርሃት የተነሳ እምነትን አጉድሎ፥ መክሊት ደብቆ የተገኘውን፥ ክፉና ሐኬተኛ አገልጋይ ቅጣትም አብረን ልናይ ግድ ነው።  አገልግሎት በሰው ብቻ ሳይሆን በእግዚአብሔር ፊት በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ የሚደረግ፥ ታላቅ ኃላፊነትንና ታማኝነትን የሚጠይቅ ስለ ሆነ ለአገልግሎት መመረጥ ቀላል ነገር አይደለም። ተመርጠው እንደ እግዚአብሔር አላማና እቅድ እንዲሁም ፈቃድ ለሚታዘዙ በረከት ሲኖረው ተመርጠው ለማይታዘዙ ደግሞ መርገም በውስጡ አለበት።

ለምሳሌ ያህል የእሥራኤል የመጀመሪያ ንጉሥ የነበረው ሳኦል የእግዚአብሔርን ትእዛዝ በመጣሱ የሰይፍ ሰለባ፥ የጦር ራት ሆኖ በትረ መንግሥቱ ለዳዊት ተሰጥቶበታል።  የአገልግሎት ነገር ሲነሳ ምንጊዜም የሚታወስ የሁለት እኅትማማቾች የማርታና የማርያም ታሪክ አለ። ማርታ ወደ ኩሽና የገባችው ጌታን ለማስደሰት ነበር። ይሁንና ማንን እንደምታገለግል በመዘንጋቷ በመጀመሪያ ያደረገችው እኅቷን ማሳጣትና በእርሷ ላይ መቆጣትን ነበር። አጀማመሯ በቅን ልብ ይሁን እንጂ ቀስ በቀስ ‘ጥሩ ሠራተኛና አገልጋይዋ ማርታ’ ተብላ ለራሷ ሞገስን ለማግኘት ፍላጎታዊ ዝንባሌ አድሮባት ነበር። ግን የፈለገችውን አላገኘችም። (ሉቃ.10፥40)  ወገኖች፥ በአገልግሎት ላይ ተሠማርተን ማን አገልጋይ፥ ማን ተገልጋይ እንደ ሆነ ከረሳንና የቆምንበትን አገልግሎት ዋና ምክንያት ቸል ካልን አገልግሎታችን ለእግዚአብሔር ሳይሆን ለራሳችን ይሆናል። በዚያ ደግሞ እግዚአብሔር አይከብርም። ማርታ የገጠማት ይህ ችግር ነበር።  አምላክ በአገልግሎታችን የሚደሰተው ንጹሕ በሆነ ትኁት ልብ፥ ካለማጉረምረም ደስ ብሎን እንጂ እንደ ማርታ በማጉረምረም፥ በመጨነቅ፥ በመባከን፥ በመታወክ፥ በነቀፌታና በማማረር አይሁን።

እኛ የዓለም ብርሃን ነን። (ማቴ፥5፥14) ሌሊቱ አልፎአል፥ ቀኑም ቀርቦአል። እንግዲህ የጨለማውን ሥራ አውጥተን የብርሃንን ጋሻ ጦር እንልበስ። (ሮሜ.13፥12) ያየነውን የሰማነውን የወንጌልን ዜና እየተናገርን፥ (ሐዋ.4፥20) በአገልግሎታችን በመበርታት እርሱ ሊልቅ እኛ ግን ልናንስ ያስፈልጋልና (ዮሐ.3፥30) እግዚአብሔርን እንፍራ፥ ያደረገልንንም ታላቅ ነገር አይተናልና በፍጹም ልባችን በእውነት እናምልከው፥ እናገልግለው። (1ኛ ሳሙ.12፥24) ።  እንግዲህ እኛ አገልጋይ ነን የምንለው፥ ያለንን ሁሉ ትተን ካልተከተልነው ደቀ መዝሙሩ፥ አገልጋዮቹ ልንሆን አንችልምና (ሉቃ.14፥33) የኃጢአት ጓዝ፥ የርኩሰት ሸክም ይዘን ለአገልግሎት በኃያሉ እግዚአብሔር ፊት ካለ ንስሐ ለመቅረብ አንድፈር።  “እነሆ፥ በቶሎ እመጣለሁ፥ ለእያንዳንዱም እንደ ሥራው መጠን እከፍል ዘንድ ዋጋዬ ከእኔ ጋር አለ፥” ብሏልና (ራእ.22፥12) አገልግሎታችን ለጌታ፥ ስለ ጌታ ይሁን።

እንደ ገብር ኄር ታሪክ ምሳሌ መሰረት እያንዳንዱ ክርስቲያን በመጭዋ ዘለዓለማዊ የእግዚአብሔር ቤት፥ መንግሥተ ሰማይ ሊያገኘው የሚገባ ስፍራ፥ ሊኖረው የሚገባ አገልግሎት በዚህ በምድር ላይ ተሰጥቶት ባለው ታማኝነትና አገልግሎት ይወሰናል። (ማቴ.25፥19) ለአማኝ የሚሰጠው ዘለዓለማዊ ሽልማትና ስፍራም አሁን በምድር፥ በሕይወት ሳለ በእጆቹ የያዛቸው በአደራም የተሰጡት መክሊቶች ወሳኝነት አላቸው። ከሩጫው ፍጻሜ በኋላ የሚሰጠው ርስትና የሥልጣን ማዕረግም አሁን ባለው የአገልግሎት መክሊቶች ትርፍ መጠንና ይዘት ነው። (ሉቃ.22፥24-30)

በመጨረሻም፥ ኢየሱስ ክርስቶስ በራሱ አንደበት፥ “…ማንም ከእናንተ ታላቅ ሊሆን የሚወድ የእናንተ አገልጋይ ይሁን። ከእናንተም ማንም ፊተኛ ሊሆን የሚወድ የሁሉ ባሪያ ይሁን፥” ሲል አሳስቦን ሄዷልና (ማር.10፥43-44) በአገልግሎታችን የሚገኘው የመክሊት ትርፍ እግዚአብሔርን ለማስደሰት፥ ክርስቶስን ለማክበር፥ ሰውንም ለመጥቀም ብቻ ይሁን። “እኔ” የአገልግሎት ጠላት፥ መክሊት የሚያስቀብር ሐኬት ነውና ከእርሱ እንራቅ።

 

መደምደሚያ

በዚህ ሳምንት የመክሊትን፥ የአገልግሎትን ትርጉም አሰላስሎ በማጤን፥ “ጌታን በምንና እንዴት ላገልግለው?” ብለን በሰጠን ነገር ሁሉ በትዳራችን፥ በእውቀታችን፥ በገንዘባችን፥ በጊዜያችን፥ በሥራችን ወ.ዘ.ተ… በታማኝነት ለአገልግሎት ተነቃቅቶ ለመነሳት የምንጾምበትና የምንጸልይበት እንዲሆን እግዚአብሔር ይርዳን። አሜን!

 

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

የእግዚአብሔር አገልጋይ

መስፍን ሙላት

ቨርጂንያ

፳፻፬ ዓ.ም